ርእሰ ባሕታውያን ሊቀ አእላፍ ቆሞስ አባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም ማናቸው ?

መስራችና አበምኔት

ርእሰ ባሕታውያን ሊቀ አእላፍ ቆሞስ አባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር ዞን በደራ ወረዳ አንበሳሜ ከተማ አካባቢ በ1951 ዓ.ም መስከረም 1 ቀን ተወለዱ፡፡ ከሕፃንነታቸው ጀምሮ የነበራቸው ምኞት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክረስቶስ በቅዱስ ወንጌል ሊከተኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ ማቴ.16÷24 ብሎ እንደተናገረው በምነና ሕይወት የኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ተሸክመው ስለስሙ መከራ መቀበል፣ ወንጌልን ለመላው ዓለም መስበክ፣ እንደ ቀደሙት ቅዱሳን አባቶችና እናቶች ገዳማትን መመስረትና ታሪክ መሥራት፣ በበሽታና በተለያየ አካላዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ውስጥ ስለሚኖረው የዓለም ሕዝብ እየጸለዩና በእንባና በለቅሶ እግዚአብሔርን እየለመኑ ለመኖር ስለነበር እግዚአብሔር በምነና አብረዋቸው የሚኖሩ መንፈሳዊ አባት እንዲሰጣቸው ዘወትር ይለምኑ ነበር፡፡ በዚህ የልጅነት ዘመናቸውም በ1964 ዓ.ም መስከረም 1 ቀን ስለ ወንቅ እሸት ገዳም እንደገና መመስረትና ብዙ ተአምራት እንደሚሠራበት እግዚአብሔር በራእይ ገልጾላቸዋል፡፡፡፡ አባታችን አባ ዮሐንስ እንዲህ እግዚአብሔርን እየለመኑ ሲኖሩ በተመሳሳይ ሁኔታ አባ ገብረ ማርያም የተባሉ በመላው ኢትዮጵያ የታወቁ ታላቅ ባሕታዊ ይሄንን ዓለም ንቆ የተወና በትጋት በመንፈሳዊ ፍቅር ጸንቶ የሚያገለግላቸው መንፈሳዊ ልጅ አጥተው እግዚአብሔር አምላክ አገልጋይ እንዲሰጣቸው ይጸልዩ ነበር፡፡ በመጨረሻ እግዚአብሔር የባሕታዊውን የአባ ገብረ ማርያምንና የአባታችን የአባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያምን ጸሎት ሰምቶ  መልአኩን ልኮ ባሕታዊውን አባ ገብረ ማርያምን አባታችን አባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም ቀንና ሌሊት ወደሚያገለግሉበትና ወደሚጸልዩበት ቤተ ክርስቲያን ላካቸው፡፡ በዚህ መሠረት ጥቅምት 30 ቀን በ1965 ዓ.ም ባሕታዊው አባ ገብረ ማርያም አባታችን አባ ዮሐንስ ወደሚኖሩበት ቦታ በመሄድ እግዚአብሔር እንደላካቸው ሲነግሯቸው አባታችን አባ ዮሐንስም ቀደም ብሎ ይህ ነገር ከእግዚአብሔር ተገልጾላቸው ስለነበር በዚያው ቀን የተወለዱበትን ቦታና ቤተሰቦቻቸውን ትተው መንነው ከአባ ገብረ ማርያም ጋር ሄዱ፡፡ እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ ማቴ.19÷27

የአባታችን የአባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም የምነና ሕይወት

አባታችን አባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም ከሕፃንነታቸው ጀምሮ የክርስቶስን መስቀል ተሸክመው መከራ ለመቀበል በነበራቸው ጽኑ ፍላጎት ከአባ ገብረ ማርያም ጋር በእግዚአብሔር ፈቃድ እስከተገናኙበት ቀን ድረስ የልጅነት ዘመናቸውን እግዚአብሔርን በማገለግለል ተወስነው ምንም የተወለዱበትን ቦታ ባይለቁ ባሉበት ሆነው የእግዚአብሔርን ፈቃድ እየጠበቁ በምነና ሕይወት ይኖሩ ነበር፡፡ ከታላቁ ባሕታዊ ከአባ ገብረ ማርያም ጋር ከተገናኙ በኋላም ኢያሱ ነቢዩ ሙሴን፣ ኤልሳዕም ነቢዩ ኤልያስን እንዳገለገሉ ዘኁ.11÷28፣ 2ኛ ነገ.2÷2 በብሕትውና ሕይወት ጸንተው አባ ገብረ ማርያምን  በትሕትና ተግተው በማገልገል እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወሩ አብያተ ክርስቲያናትን በመሥራትና በማሠራት፣ ለካህናትና ለምእመናን ወንጌልን በመስበክ ኖረዋል፡፡ ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፤ እባቦችን ይይዛሉ፥ የሚገድልም ነገር ቢጠጡ አይጎዳቸውም፤ እጃቸውን በድውዮች ላይ ይጭናሉ እነርሱም ይድናሉ። ማር. 16÷17 ተብሎ እንደተጻፈ አባታችን በምነና ዘመናቸው በተዘዋወሩበት ቦታ ሁሉ በሚባርኩት ጸበልና በተሰጣቸው የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ድውያን ተፈውሰዋል፤ በሰይጣን ማሰሪያ የታሰሩ ተፈትተዋል፤ ከህገ እግዚአብሔር ርቀው በተበላሸ ሕይወት ውስጥ የነበሩ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰዋል፤ በተለያየ ችግር ውስጥ የወደቁ ከችግራቸው ወጥተዋል፤ ብዙ ተአምራቶች ተሠርተዋል፡፡ አባታችን አባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም በዚህ ሁኔታ በብሕትውና እግዚአብሔርንና ሕዝብን እያገለገሉ ሲኖሩ ዋና ምኞታቸው እንደቀደሙት አባቶችና እናቶች ገዳማትን መመስረትና መነኮሳትን መሰብሰብ እንዲሁም ድውያን ሲፈወሱ ማየት፣ ከእግዚአብሔር ሕግ የወጡት በስብከተ ወንጌል ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ማድረግና ለሀገርና ለሕዝብ የሚሆን ታሪክ መሥራት ስለነበር ገዳማትን ለመመስረት ዘወትር እግዚአብሔርን ተግተው ይለምኑ ነበር፡፡  

የአድያመ ዮርዳኖስ ወንቅ እሸት ቅዱስ ገብርኤል አንድነት ገዳም አመሠራረት

አባታችን አባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም ገዳማትን ለመመስረትና መናንያንን ለመሰብሰብ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በጸሎት እየተጠባበቁ ሲኖሩ በ1993 ዓ.ም ቅዱሳን ቦታዎችን ለመሳለም ለመስቀል በዓል ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ሄዱ፡፡ በዚያም ሳሉ መስከረም 19 ቀን ከእግዚአብሔር ዘንድ ‹‹የኢየሩሳሌም ሰዎች በዚህ እንድትኖር ይለምኑሃል፤ ነገር ግን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰህ ወንቅ እሸት ቅዱስ ገብርኤል አንድነት ገዳምን ትመሰርታለህ፡፡ ያን ገዳም ስትመሰርትም ብዙ ጠላቶች ይነሱብሃል፡፡ የቀረቡህ ይርቁሃል፣ ያመንሃቸው ይከዱሃል፡፡ ይህ ሁሉ የመነኮሳት እድል ፈንታቸው ነውና ጽና፤ አሁንም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰህ ታሪክ እንድትሠራ አዝዤሃለሁ›› የሚል ቃል ስለተነገራቸው  ቅዱሳን ቦታዎችን ተዘዋውረው ከተሳለሙ በኋላ እንደ እግዚአብሔር ቃል ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ፡፡ ወንቅ እሸት ገዳም ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት በሺህ የሚቆጠሩ መነኮሳት ይኖሩበት እንደነበር ይነገራል፡፡ በ1521 ዓ.ም አካባቢ በቤተ ክርስቲያን ላይ የተነሳው ግራኝ አህመድ መነኮሳቱን ጨፍጭፏቸዋል፤ ገዳሙንም አፍርሶታል፡፡ ገዳሙ ከፈረሰ በኋላ ሽፍቶችና ሌቦች በመሰባሰብ ጫካውን መኖሪያቸው አድርገው የጎጃምና የጎንደርን ሕዝብ ከብትና ንብረት እየዘረፉ ሲበሉበት ኖረዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በቦታው የሚያልፍ ሰው ሁሉ በሽፍቶችና በሌቦች እየተደበደበ ስለሚዘረፍ በአካባቢው ማንኛውም ሰው አልፎ ለመሄድ አይችልም ነበር፡፡

አባታችን አባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም ኢየሩሳሌምን ተሳልመው ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ከእግዚአብሔር ያገኙት ቃል እስኪፈጸም ድረስ በእንባና በለቅሶ በጸሎት ተግተው ሲጠባበቁ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ በወንቅ እሸት ገዳም ዙሪያ የሚኖሩ ሰዎች ተሰባስበውና ተፈራርመው መጥተው ገዳሙን ያቅኑት ብለው ጠየቋቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር እንደተፈቀደላቸው ሁሉ ከምድርም ከምእመናኑ፣ ከቤተ ክህነትና ከመንግስት አስፈቅደው መስቀላቸውን ብቻ ይዘው ማንም አልፎ ወደማይሄድበት የሽፍቶች ቦታ ወደሆነው ጫካ በመግባት ቀጥ ካለው ተራራ ላይ በብዙ ትግል መሬቱን ቆፍረው ትንሽ መቃረቢያ ሠርተው ጥር 5 ቀን 1994 ዓ.ም የቅዱስ ገብርኤልን ታቦት በማስገባት ገዳም የመመስረት ሥራቸውን ጀመሩ፡፡

ርእሰ ባሕታያን ሊቀ አእላፍ ቆሞስ አባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም ‹‹ቤተ ክርስቲያናችን ትለመናለች እንጅ አትለምንም›› የሚል ጽኑ ዓላማ ይዘው ቤተ ክርስቲያኑን ለመሥራት በመነሳት መሐንዲሶችን አስመጥተው ቦታውን እንዲያዩ አድርገው የነበረ ቢሆንም መኃሐንዲሶች ግን እዚህ ተራራ ላይ ቤተ ክርስቲያን መሥራት አይቻልም በማለት ተመልው ሄደዋል፡፡ አባታችን አባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም ግን ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንጅ የሰው ፈቃድ አይደለም ብለው ቀንና ሌሊት ተራራውን እራሳቸው በአዷማ በመቆፈር እንዲሁም መጽሐፎችንና የመዝሙር ካሴቶችን በማሳተም የቀን ሠራተኞችን በገንዘብ ቀጥረው በማሠራት የመኪና መንገድ፣ የመብራትና የስልክ አገልግሎት ሳይኖር ተራራውን በመቆፈርና ገደሉን በመሙላት ሜዳ አድርገው ሲሚንቶ፣ ብረታ ብረትና አስፈላጊው ለግንባታ የሚውል ቁሳቁስ ሁሉ በእንስሳትና በሰው ሸክም ተጓጉዞ የወንቅ እሸት ቅዱስ ገብርኤል አንድነት ገዳም ቤተ ክርስቲያንን የሥራ ቀናት ተቆጥረው በሰባት ወር ከአስር ቀናት ብቻ ሠርተው በመጨረስ ጥር 19/1998 ዓ.ም አስመርቀዋል፡፡

ከዚያም በኋላ ሥራቸውን በመቀጠል የደብረ ዘይት አትሰድም ማርያም የሴቶች አንድነት ገዳም ቤተ ክርስቲያንን በአራት ወራት ብቻ የሕንጻ ግንባታውን በማጠናቀቅ ጥር 21/2000 ዓ.ም፣  የደብረ ልዑላን ግና ቅዱስ ቂርቆስ የወንዶች አንድነት ገዳም ቤተ ክርስቲያንን በ7 ወራት ሥራውን በማጠናቀቅ ጥር 15/2003 ዓ.ም፣ የቃለ አዋዲ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የወንዶች አንድነት ገዳም ቤተ ክርስቲያንን ሰኔ 15/2005 ዓ.ም አስመርቀዋል፡፡ በተጨማሪም በምእመናኑ ተማጽኖ መንበረ ጸሐይ አንበሳሜ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን በአስራ አንድ ወራት ሠርተው በ2006 ዓ.ም በማስመረቅ መዝሙረኛው ዳዊት ስምህን ለሚፈሩ ርስትን ሰጠሃቸው መዝ. 60÷5 እንዳለ በአስር ዓመታት ውስጥ አምስት ቤተ ክርስቲያናትን በመሥራትና ገዳማትን በመመስረት ለዘለዓለም የሚኖር ታላቅ ታሪክ አስቀምጠዋል፡፡

ወንቅ እሸት ቅዱስ ገብርኤል አንድነት ገዳም

የወንቅ እሸት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ጥር 5 ቀን 1994 ዓ.ም የቅዱስ ገብርኤልን ታቦት በማስገባት ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ፡፡ የሕንጻ ግንባታ ሥራው በሰባት ወር ከአስር ቀናት ተጠናቅቆ ጥር 19/1998 ዓ.ም ተመረቀ፡፡ በዚህ ገዳም ታሕሳስ 19 እና ሐምሌ 19 የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል ከመላው ዓለም በሚመጡ ምእመናን በልዩ ሁኔታ ይከበራል፡፡ 

ቃለ አዋዲ ቅዱስ ዮሐንስ የወንዶች አንድነት ገዳም

የቃለ አዋዲ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የወንዶች አንድነት ገዳም ቤተ ክርስቲያን ሰኔ 15/2005 ዓ.ም ተመረቀ፡፡ በዚህ ገዳም ቅዱስ ዮሐንስ ቃል ኪዳን የተቀበለበት መስከረም 1 እና የተወለደበት ሰኔ 30 በየዓመቱ በደማቅ ሁኔታ ይከበራል፡፡

ደብረ ልዑላን ግና ቂርቆስ የወንዶች አንድነት

የደብረ ልዑላን ግና ቅዱስ ቂርቆስ የወንዶች አንድነት ገዳም ቤተ ክርስቲያን የሕንጻ ሥራው በ7 ወር ውስጥ ተጠናቅቆ ጥር 15/2003 ዓ.ም ተመረቀ፡፡ በገዳሙ ጥር 15 የሰማዕቱ የቅዱስ ቂርቆስና የእናቱ የቅድስት ኢየሉጣ፣ ሕዳር 26 የአቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሀንና ሚያዝያ 30 የወንጌላዊው የቅዱስ ማርቆስ ዓመታዊ ክብረ በዓላት በታላቅ ስነ ስርዓት ይከበራሉ፡፡

ደብረ ዘይት ማርያም የሴቶች አንድነት ገዳም

የደብረ ዘይት አትሰድም ማርያም የሴቶች አንድነት ገዳም ቤተ ክርስቲያን  የሕንጻ ግንባታ ሥራ በአራት ወራት ብቻ አልቆ ጥር 21/2000 ዓ.ም ተመረቀ፡፡ በገዳሙ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት የሚታሰብበት የደብረ ዘይት (የዓቢይ ጾም ግማሽ ) ክብረ በዓል በደማቅ ሁኔታ የሚከበር ሲሆን እንዲሁም ጥር 21 የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በአል ይከበራል፡፡

አንበሳሜ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን

መንበረ ጸሐይ አንበሳሜ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ምእመናኑ ባቀረቡት የይሥሩልን ጥያቄ የሕንጻ ግንባታ ሥራው በአስራ አንድ ወራት ተጠናቆ በ2006 ዓ.ም ተመረቀ፡፡

መነኮሳት በአድያመ ዮርዳኖስ ወንቅ እሸት ቅዱስ ገብርኤል አንድነት ገዳም

ርእሰ ባሕታውያን ሊቀ አእላፍ ቆሞስ አባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም በ1994 ዓ.ም ብቻቸውን ወደ ጫካው ገብተው አድያመ ዮርዳኖስ ወንቅ እሸት ቅዱስ ገብርኤል አንድነት ገዳምን መመስረት ከጀመሩበት ሰዓት ጀምሮ ዓለምን ንቀው በመተው በምነና ለመኖር የፈለጉ መናንያንና መናንያት በዙሪያቸው መሰባሰብ ጀመሩ፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአድያመ ዮርዳኖስ ወንቅ እሸት ቅዱስ ገብርኤል አንድነት ገዳም በአባታችን በአባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም አበምኔትነት ስር የሚኖሩና በአንድነት ገዳም ስርዓት የሚተዳደሩ ከአራት መቶ በላይ መነኮሳትና መነኮሳይያት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ መነኮሳት ከገዳሙ መሥራችና አበምኔት በተማሩት መሰረት ከጸሎት በሚተርፋቸው ጊዜ በዘመናዊ የሽመና ሥራ፣ ከብቶችን፣ በጎችንና ፍየሎችን በማርባት፣ ንብ በማነብና በመሳሰሉት የሥራ ዘርፎች ተሠማርተው ጠንክረው በመሥራት እግዚአብሔርን እያገለገሉ ይኖራሉ፡፡ በዚህ በመጨረሻው ዘመን በእግዚአብሔር ፈቃድ በርእሰ ባሕታውያን ሊቀ አእላፍ ቆሞስ አባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም የተመሰረተው ይህ ገዳም ለእምነት፣ ለፀበልና ለመስቀል እየተባለ ገንዘብ የማይከፈልበት፣ ስብከተ ወንጌል የማይቋረጥበት፣ የእግዚአብሔር ተአምራትና ድንቅ ሥራ ዘወትር የሚታይበትና ፍጹም የሆነ የፍቅር አገልግሎት ለምእመናን የሚሰጥበት በመሆኑና ባለው ጠንካራ የሥራ ባሕልና የልማት ተሞክሮ ለተለያዩ ገዳማትና አድባራት እንዲሁም ለመላው ዓለም ሕዝብ አርአያና ምሳሌ ሆኖ ይገኛል፡፡

በወንቅ እሸት የሚሠራ መቁጠሪያ

የወንቅ እሸት ገዳም መነኮሳት

መንፈሳዊ አገልግሎቶች በአድያመ ዮርዳኖስ ወንቅ እሸት ቅዱስ ገብርኤል አንድነት ገዳም

ርእሰ ባሕታውያን ሊቀ አእላፍ ቆሞስ አባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም ከልጅነታቸው ጀምሮ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ያደረባቸው አባት በመሆናቸው በምነና ዘመናቸው  በጸሎታቸው ድውያን ሲፈወሱ እንደኖሩት ሁሉ ወንቅ እሸት ቅዱስ ገብርኤል አንድነት ገዳምን ለመመስረት ሲነሱ በ1994 ዓ.ም አንዴ ተራራውን በአራቱ ማእዘናት በስላሴ ስም በበትረ መስቀላቸው ባረኩት፡፡  ተራራው ከተባረከበት ሰዓት ጀምሮም በእግአዚብሔር ቸርነት፣ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ በቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት፣ በአባታችን በአባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም ጸሎትና እንባ በኤች አይ ቪ ኤድስ፣ በካንሰር፣ በደም ግፊት፣ በስኳርና በመሳሰሉት በተለያዩ ከባድና አስፈሪ በሽታዎች የታመሙ ሁሉ ከማንኛውም በሽታ እየተፈወሱ፣ በሰይጣን ማሰሪያ በድግምት በመተት የተተበተቡ እየተፈቱ፣ ልጅ ያጡ በወንቅ እሸት ተማጽው እየወለዱ፣ በረከት ያጡ በረከት እያገኙ፣ በጫት፣ በሲጋራ፣ በአሺሽ፣ በስካርና በተለያዩ ደባል ሱሶችና የኃጢአት ሥራዎች ተሰማርተው የኖሩ አባታችን አባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም  ዘወትር በሚሰጡት ስብከተ ወንጌል አእምሯቸው ተስተካክሎ፣ ልቡናቸው ተመልሶ እግዚአብሔርን አውቀው ለሀገራቸው ለኢትዮጵያ ጥሩ ዜጋ፣ ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታቸው እውነተኛ ክርስቲያን፣ ለማህበረሰቡ ጥሩ ስነ ምግባር ያላቸው ሰዎች እየሆኑ ሁሉም በአንድነት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ይገኛሉ፡፡ አባታችንም እግዚአብሔር በሰጣቸው ጸጋ ከዓመት እስከ ዓመት ሃያ አራት ሰዓት ያለ እረፍት ሕዝቡን በስብከተ ወንጌል፣ በዝማሬ፣ በፈውስ ስርዓት እያገለገሉ ያሉ ሲሆን በተጨማሪም በመላው ዓለም እየተዘዋወሩ ወንጌልን ይሰብካሉ፡፡

የአባታችን የአባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም የበጎ አድራጎት ሥራዎች

ርእሰ ባሕታውያን ሊቀ አእላፍ ቆሞስ አባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ታሪክ ለመሥራት በነበራቸው ጽኑ ፍላጎት ከእግዚአብሔር ለምነው ባገኙት የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ገዳማትን ከመመስረታቸው በተጨማሪ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በ2011 ዓ.ም በአንበሳሜ ከተማ ዘመናዊ ትምሕርት ቤት ሠርተው አስረክበዋል፡፡ በዚሁ ዓመት በሰሜን ጎንደር የእርስበርስ ግጭት ለተፈናቀሉ ወገኖች ከመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው ጋር በመተባበር የአንድ ሚሊዮን (1,000,000) ብርና የ300 ኩንታል እህል ድጋፍ አድርገዋል፡፡ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ላይ እየደረሰ ባለው ስደት ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን እንዳታጣ የሊቃውንትን ስደት ለማስቆም በደራ ወረዳ ውስጥ ለሁሉም የአብነት መምህራን ከ2012 ዓ.ም ከህዳር ወር ጀምሮ በቋሚነት ደመወዝ እየከፈሉ ያሉ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ በመገኘት ለህግ ታራሚዎች ግብዣ በማዘጋጀትና ወንጌልን በመስበክ እግዚአብሔርንና ሕዝብን በቅንነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

አባታችን በአንበሳሜ ከተማ ያሠሩት ት/ቤት

ለሊቃውንት ደመወዝ ለመክፈል የተደረገ ጉባኤ

የገዳሙ አድራሻ

አድያመ ዮርዳኖስ ወንቅ እሸት ቅዱስ ገብርኤል አንድነት ገዳም የሚገኘው በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር ዞን በደራ ወረዳ ልዩ ስሙ ወፍ አርግፍ ታምሬ በተባለ ቀበሌ ነው፡፡ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያም ውጭ ከመላው ዓለም ለምትመጡ ሁሉ በአውሮፕላንም ሆነ በመኪና በመጀመሪያ ወደ ባሕር ዳር ከተማ መድረስ ይጠበቅባችኋል፡፡ ባሕር ዳር ከደረሱ በኋላ ወደ ወንቅ እሸት ገዳም ለመድረስ ከባሕር ዳር እስከ ጢስ አባይ (በዓለም የታወቀው የጢስ አባይ ፏፏቴ የሚገኝበት ቦታ) 30 ኪ.ሜ የመኪና መንገድ ሲሆን ከጢስ አባይ እስከ ገዳሙ የ45 ደቂቃ የእግር ጉዞ ነው፡፡ በእግር መጓዝ የማትችሉ ጢስ አባይ ስትደርሱ የገዳሙ የንዋየ ቅድሳት መሸጫ ሱቅ ስላለ ከሱቁ ካሉት መነኮሳት ጋር በመነጋገር በቅሎ ከገዳሙ እንዲመጣላችሁ ማዘዝ ትችላላችሁ፡፡

ማሳሰቢያ፡-

    ከመላው የዓለም ክፍል የምትመጡ ሁሉ ከተነሳችሁበት ቦታ ጀምሮ ወደ ገዳሙ እስክትደርሱ ድረስ ወደ ገዳሙ እንዳትመጡ በሰይጣናዊ የቅንአት መንፈስ ተነሳስተው ብዙ የሐሰት ወሬ የሚያወሩ ስላሉ በየመንገዱ፣ በምታድሩባቸው ሆቴሎች፣ በአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ በአውቶብሶችና በታክሲዎች ውስጥና በመሳሰሉት ቦታዎች ስለ ወንቅ እሸት ገዳምና ስለ አባታችን ስለ አባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም የሚነገራችሁን የተለያየ አሉባልታና የስም ማጥፋት ዘመቻ አሸንፋችሁ አልፋችሁ መምጣት ይጠበቅባችኋል፡፡

Share on social media

Facebook
WhatsApp
Twitter
Telegram
Email

ስልክ:-

+251 915555744

+251 911319999

ገዳሙ የሚገኝበት አድራሻ:-

ከባሕር ዳር … ጢስ አባይ 30 ኪ.ሜ

ከጢስ አባይ … ወንቅ እሸት የ45 ደቂቃ የእግር መንገድ