መምህር ንዋይ አቢዩ ይባላል፤ በአድያመ ዮርዳኖስ ወንቅ እሸት ቅዱስ ገብርኤል አንድነት ገዳም የተደረገለትን ግሩም ተአምር እንዲህ ሲል መስክሯል፡፡ እኔ የመጣሁት ከአዴት ወረዳ ከቀበሌ 03 ሲሆን በመምህርነት እየሠራሁ እየኖርኩ እያለሁ የእራሴን ማንነት ለማወቅ ወደ ሆስፒታል በመሄድ ስመረመር በተደጋጋሚ የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽተኛ ነህ የሚል የሞት ዜና ተነገረኝ፡፡ እኔም ለሁለት ዓመታት ተስፋ ቆርጬ በኀዘን ከኖርኩ በኋላ [read more] በወንቅ እሸት ገዳም ሕመምተኞች ሁሉ ከማንኛውም በሽታ እንደሚፈወሱ ሰምቼ መጥቼ ስጠመቅ ሰንብቼ ሄድኩኝ ነገር ግን ብመረመርስ አለብህ ቢሉኝስ እያልኩ ፈራ ተባ እያልኩ ሳልመረመር ቀናት አለፉ:: እንዲህ ድኜ ይሁን አልዳንኩ ይሁን? በማለት እየተጠራጠርኩኝ በነበረበት ወቅት÷ አንድ ቀን እንደተኛሁ በሕልሜ ጸሐይ በነጭ ደመና ተከባ በሰረገላ ተጭና ወደ እኔ ትመጣለች፤ እኔም የማየው ሆኖ የማያውቅ ነገር አስደንግጦኝም አስገርሞኝም፣ ምንድነው እየሆነ ያለው ጸሐይ ወደ እኔ የምትሮጠው ለምንድነው እያልኩ ሳወጣ ሳወርድ ድንገት ከጸሐይዋ ውስጥ አባታችን አባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም ሰማያዊ ቀሚስ ለብሰው፣ በሰፊ የጠፍር መታጠቂያ ታጥቀው፣ መስቀልና ጭራቸውን ይዘው ይወጣሉ፤ እኔም ስለምወዳችው አባታችን አባ ዮሐንስ! አባታችን አባ ዮሐንስ እያልኩ ስደነቅ ከጸሐይዋ ሰረገላ ወርደው ወደ እኔ በመምጣት አይዞህ ልጄ አትጠራጠር ከበሽታህ ድነሃል ሂድና ተመርመር አትፍራ ብለው ባረኩኝ፡፡ የማያቸው ልክ በሥጋ እንደ ማያቸው ሆነው ነበር ከእንቅልፌ ስነቃ ግን ህልም ነበር፤ ያየሁት ነገር ሁሉ አስደነቀኝ፤ ተደሰትኩም፡፡ ወዲያው ተነስቼ በመጀመሪያ አዴት ጤና ጣቢያ ስመረመር ኤች አይ ቪ ኤድስ የለብህም ተባልኩ፤ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ባሕር ዳር በመሄድ የኤች አይ ቪ ኤድስ ታማሚዎች ሁሉ ክትትል ወደሚያደርጉበት ሀን ጤና ጣቢያ በመሄድ ስመረመር አሁንም ኤች አይ ቪ ቫይረስ በደምህ ውስጥ የለም የሚል አዲስ ዜና አዲስ የምስራች ሰማሁ ደስ ብሎኛል ደስ ይበላችሁ፡፡ በእውነት የእግዚአብሔር ሥራው ድንቅ እና ግሩም ነው የተደረገልኝን ለመናገር አንደበት ያጥረኛል እኚህን አባት የሰጠን የአባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም አምላክ ሕያው እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፡፡ [/read]